13/01/2021
የምግብ ማቀዝቀዣ (ፍሪጅ) እንዴት ይሠራል?
በማቀዝቀዣው ዑደት ውስጥ አምስት መሠረታዊ አካላት አሉ፡፡
1- ፈሳሽ ማቀዝቀዣ / Fluid Refrigerant
2- የማቀዝቀዣውን ፍሰት የሚቆጣጠር መጭመቂያ / Compressor
3- ከትነት ወደ ፈሳሽ ቀያሪ (ከማቀዝቀዣው ውጭ) / Condenser
4- የትነት ቀያሪ (በማቀዝቀዣው ውስጠኛ ክፍል ላይ) Evaporator
5- የማስፋፊያ መሳሪያ / Expansion Device or Valve
እነዚህ አምስት ክፍሎች ምግብዎን ለማቀዝቀዝ እንዴት እንደሚገናኙ እነሆ፡
1. መጭመቂያው / Compressor የሪፍሪጅራንቱን እንፋሎት በማመቅ፣ ግፊቱን ከፍ በማድረግ በማቀዝቀዣው ውጭ ወዳሉት ጥቅልሎች ውስጥ ይገፋዋል፡፡ ይፍ ትነት ሲታመቅ ሙቀቱ ይጨምራል።
2. በCondenser ጥቅልልዎች ውስጥ ያለው ሞቃት ጋዝ በወጥ-ቤቱ ወይም በኪችኑ ውስጥ ባለው ቀዝቃዛ አየር ሲቀዘቅዝ ፈሳሽ ይሆናል፡፡ ተለቅ ያሉ ፍሪጆች፣ Cooling Fan ወይም አየር የማቀዝቀዣ ማራገቢያ በመጠቀም ይቀዘቅዛሉ።
3. አሁን በቀጭን ትቦ በከፍተኛ ግፊት በፈሳሽ መልክ የመጣው ሪፍሪጅራንት ወደሰፊ ትቦ ወዳለው የትነት ቀያሪ ጥቅልሎች/ Evaporator በማስፋፊያው ቫልቭ በኩል ሲፈስ ይቀዘቅዛል።
• የማስፋፊያውን ቫልቭ እንደትንሽ ቀዳዳ ማሰብ ይችላሉ፡፡ ከቀዳዳው በአንዱ በኩል ከፍተኛ ግፊት ያለው የሪፍሪጅራንት ፈሳሽ ነው፡፡ በቀዳዳው ሌላኛው በኩል ዝቅተኛ ግፊት ያለው አካባቢ ነው (ምክንያቱም መጭመቂያው/ Compressor ከዚያ ጎን ጋዝ ስለሚስብ ነው። ፈሳሹ ሪፍሪጅራንት በቀዳዳው አልፎ ወደ ዝቅተኛ ግፊት ወዳለው ጥቅልል ሲያልፍ ወዲያውኑ የሙቀት መጠኑ ዝቅ ይላል። ይህ የማቀዝቀዣውን ውስጠኛ ክፍል እንዲቀዘቅዝ ያደርገዋል፡፡
4. በዚህም ጊዜ የተነነው ሪፍሪጅራንት በማቀዝቀዣው ውስጥ ያለውን ሙቀት ይወስዳል፡፡ ይህ የሚሆነው ሙቀት ከሞቃታማ ስፍራ ወደ ቀዝቃዛ ስፍራ ስለሚፈስ ነው።
5. በመጨረሻም ሪፍሪጅራንቱ በማቀዝቀዣው ውስጥ ያለውን ሙቀት ይዞ ዑደቱን በድጋሚ ወደሚጀምርበት ወደ መጭመቂያው ይመለሳል።